አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት ለ31ኛ ጊዜ አመርቂ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፣ በዓመቱ ከታክስ በፊት ብር 1 ቢሊዮን በላይ አተረፈ። በበጀት ዓመቱ የተገኘው ያልተጣራ ትርፍ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 27 በመቶ በላይ እድገት ያሳየ መሆኑ በኩባንያው የባለአክሲዮኖች 31ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገልጿል። የአዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ የባለአክሲዮኖች 31ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ተካሂዷል፡፡ ኩባንያው በተጠናቀቀው ሂሳብ ዓመት የተቀዳጀው ትርፍ በኢትዮጵያ የግል ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ታሪክ ከዚህ ቀደም ያልተመዘገበና ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነ፣ ከቢሊየን ብር የተሽገረ ትርፍ ሆኖ ተመዝግቧል።
በተጠናቀቀዉ በጀት አመት የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል በ38 በመቶ አድጐ ብር 2.65 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ የተፈረመ ካፒታሉም ደግሞ 4 ቢሊዮን ሆኗል፡፡
ኩባንያዉ በዋነኛ የሥራ ዘርፎች እያስመዘገበ የዕድገት ምጣኔን በተመለከተ፣ በጀነራል ኢንሹራንስ (Non-Life) የ43 በመቶ፣ በሕይወት ዘርፍ ኢንሹራንስ ደግሞ የ48 በመቶ ዕድገት በማሳካት፣ እንደዚሁም በተካፉል የ124 በመቶ ዕድገት በማስመስግብ እጅግ አኩሪ ዉጤት አስመዝግቧል። ኩባንያዉ በአሥሩ ዓመት መሪ ዕቅድ እየተመራ ይሄን እጅግ ፈጣን የሆነ የዕድገት ምጣኔ በማሣካት ተካፉልን ጨምሮ በሁሉም የሥራ ዘርፎች በድምሩ ከ4.53 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ መሰብሰብ ችሏል፡፡ በጄነራል ኢንሹራንስ ከ3.73 ቢሊዮን ብር በላይ፣ በሕይወት ኢንሹራንስ ደግሞ ከ656.27 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በተካፉል ከ156 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ችሏል። የኩባንያዉ ፈጣን እድገት እና የላቀ ስራ አፈጻጸም ሁሉን አቀፍ ዉጤት ያመጣ ሲሆን በጀነራል ኢንሹራን ከ17ቱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የገበያ መሪነቱን በሰፊ ልዩነትና የገበያ ድርሻ ለ13ኛ ዓመት ያረጋገጠ ሲሆን፣ በሕይወትና ጤና መድን (Life Assurance) ዘርፍ ደግሞ ከአጠቃላይ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ መሪነቱን ዳግም አረጋግጧል። በተጨማሪም በሸሪዓ መርህዎች በሚገዛው የተካፉል ዘርፍም ከሀገሪቱ አጠቃላይ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በአጭር ጊዜ ዉስጥ በሰፊ ልዩነት በአንደኝነት ለመምራት ያስቻለዉን አስደናቂ ዉጤት አስመስግቧል።
ኩባንያው የገበያ አድማሱን ይበልጥ ለማስፋትና ለተገልጋዩ ሕብረተሰብ ተደራሽነቱን ለማረጋገጥ አቅዶ በተንቀሳቀሰዉ መሰረት አጠቃላይ የኩባንያዉ የቅርንጫፍና የአገናኝ ቢሮዎቻች ብዛት በዓመቱ መጨረሻ 71 የደረሰ ሲሆን፣ የሽያጭ ወኪሎችን ብዛት ከ300 በላይ በማድረስ ከ100 ሺ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች ቀልጣፋና አስተማማኝ የመድን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። አዋሽ የደንበኞችን እና ሰፊዉን የሀገራችን ማህበረሰብ ያማከለ የመድን ሽፋን አገልግሎት በመስጠት ቀዳሚዉን ስፍራ የሚይዝ ኩባንያ ሲሆን አብዛኞቹ የሀገራችን ህዝቦች የተሰማሩበትን የግብርና ዘርፍ ከተፈጥሮ አደጋና ከአየር ንብረት መዛባት የሚታደገዉን የሰብል መድን አገልግሎት በዘንድሮው አመት መስጠት ጀምሯል።
በሌላ በኩል ቀደም ሲል ያበለጸጋቸውን ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሲስተሞች በመታገዝ ለደንበኞቹ አስተማማኝ የመድን ሽፋን አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ እና ለደንበኞቹ ምቹና ቀላል ለማድረግ የሚይስቺል ዘመናዊ ዲጅታል ቻናል አበልጽጎ ወደ ስራ ለማስገባት ከመጨረሻ ምዕራፍ ደርሷል። በተጨማሪም ጊዜዉ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ መፍትሄዎች ሁሉ በመጠቀም ወደ ደንበኞቹ ለመቀርብ ቆራጥ አቋም ያልው በመሆኑ ደንበኞች የተለያየ የክፍያ አማራጭ ያገኙ ዘንድ ከሀገራችን የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ አንዱ ከሆነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ (ኤም ፔሳ) ጋር በመስራት ላይ ይገኛል።
የኢንቨስትመንት ምክረ ሃሳቦችን (Proposals) አዋጭነት በጥንቃቄ በመገምገምና በመፈተሽ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ስድስት ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት ያደረገ ሲሆን፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለመደግፍ የ107.6 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዢ፣ በተጨማሪም በልማት ባንክም በ120.3 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ በመፈጸም ለሀገራችን የልማትና እድገት ጥረት የፋይናንስ ምንጭ በመሆን የበኩሉን አስተዋጽዎ አበርክቷል።
በሌላ በኩል ለዋና መ/ቤቱ ባለ 4B+G+35 ወለል ያለው ሕንፃ ግንባታ የዲዛይን ማሻሻያ ሥራ (Design revision)፣ የሾሪንግ እና የመሰረት ቁፋሮ ሥራ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ፣ የዋናዉ ህንጻ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በተጠናቀቀው የሂሳብ አመት ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢ ጥበቃ ላይ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ለተለያዩ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ተቋሟዊ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ተጥቷል። ለአብነትም አሳሳቢ የሆነዉን የአየር ንብረት ለዉጥ ለመዋጋት የናይሮቢ ድክላሬሽን (Nairobi Declaration) በመፈረም ቀዳሚ በመሆን የተሰጡ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር ላይ የሚገኝ ብቸኛው የሀገራችን ኢንሹራንስ ኩባንያ ለመሆን ችሏል። በተጨማሪም ለልዩ ልዩ የድጋፍና የልማት ዕርዳታ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት በበጀት ዓመቱ በድምሩ ከብር 30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ በማድረግ ለወገንና ለአገራዊ ጥሪዎች ምላሽ መስጠት ችሏል፡፡
በመጨረሻም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለተቀዳጀው ውጤት አስተዋፅዖ ላደረጉ ሁሉ ኩባንያዉ ከፍ ያለ ምስጋና እያቀረበ፣ በኩባንያዉ ላይ ፍፁም ዕምነት በመጣል አዋሽ ኢንሹራንስን ምርጫቸው ላደረጉና አብረውን ለሰሩ ውድና እጅግ የተከበሩ ደንበኞቻችን ታላቅ ምስጋና ያቀርባል። በቀጣይም ኩባንያዉ አገልግሎቱን ይበልጥ በማዘመን የደንበኞችን ፍላጎት ማዕከል ባደረገ ጥናት በመታገዝ አዳዲስ የአገልግሎት አይነቶችን ለገበያው በማቅረብ ደንበኞቹን ለማገልገል በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡
አዋሽ ኢንሹራንስ አ.ማ. መስከረም 20 ቀን 1987 ዓ.ም. ከመንግስት የንግድ ፍቃድ አገኘ፣ ታህሳስ 23 ቀን 1987 ዓ.ም. በይፋ ስራዉን ጀመረ። በሀገራችን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ታሪክ ለሌሎች ምሳሌ በሆነዉ ጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ የመጀመሪያዉ መሰረተ-ሰፊ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያ ነዉ። በምስረታ ወቅት ባለአክሲዮኖቹ 456 የነበሩ ሲሆኑ አሁን ላይ የባለአክሲዮኖች ብዛት 2168 ደርሷል።


